አንጾኪያ የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተክርስትያን
መተዳደርያ ደንብ
አፕሪል 2009
አንቀጽ – 1 ፡ የቤተክርስቲያኒቱ መጠሪያ ስም
ይህ ማህበረ ምእመን አንጾኪያ የኢትዮጵያውያን ወንጌላዊት ቤተክርስቲያን ተብሎ ይታወቃል።
አንቀጽ 2 – ቢሮው (ዋና ጽህፈት ቤቱ)
የማህበረ ምእመኑ (የአባላቱ )እንቅስቃሴና የተግባር ማከናወኚያው የሚሆነው በአሌክሳንድሪያ ቨርጂኒያ ነው። የቤተክርሰቲያኒቱ የሽማግሌዎች ጉባኤ እንደአስፈላጊነቱ የቤተክርስቲያኒቱ ዋና ቢሮ መለወጥ ይችላሉ፡፡
የቢሮው ለውጥ በዚህ ህገ ደንብ ላይ ይጨመራል ወይንም በማዳበሪያነት ይጨመራል፡፡
የሽማግሌዎች ጉባኤ በማንኛውም ጊዜ እንደ አስፈላጊነቱ ለዋናው ቢሮና ለአገልግሎት አስፈላጊነቱ በተረጋገጠ ጊዜ ተጨማሪ አጥቢያዎች በተፈላጊው ቦታና ሥፍራ ለማህበረ ምእመኑ መክፈት ይቻላል፡፡ ተጠሪነቱ ለዋናው ማህበረ ምእመን ይሆናል፡፡
አንቀጽ 3 – ዓላማና ተጨማሪ ተግባር
ክፍል 1 – ዓላማ
በእምነት አንቀጽ ላይ እንደተጠቀሰውና እንደተብራራው አጥቢያ ቤተ ከርስቲያኒቱ ያለ አንዳች ድርድር ዓላማዋ እውነተኛ አምልኮ፣ ምስጋና፣ አክብሮትና አድናቆት ለእግዚአብሔር ለማቅረብ፣ የክርስቶስን ጌትነትና አዳኝነት ለዓለሙ አዋጅ መናገርና መስበክ ሲሆን ይኸውም ቃሉን ያለመሸቀጥ ማስተማር፣ በጸሎትና በምልጃ የጌታን ፊት በመፈለግ ይኸውም በትህትናና በምስጋና፣ በጸሎት፣ ምሪቱን በመጠየቅ፣ ቅዱሳንን በቃሉ በማስታጠቅ በፊቱ እንዲመላለሱ እንዲያገለግሉት ለክንዋኔው ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ህብረት በማድረግ በኃይሉ ቅባት እንዲታጠቁ ማድረግ ነው (ማቴ 28፡18-20፤ የሐዋ፡ 1፡8 2፡42-46 1ቆሮ 11፡24-25፤14፡26፤ ኤፌ 4፡11-16፤ቆላ 1፡24-28፤ 1ጢሞ 4፡11)።
ክፍል 2 – ተግባር
የዚህ ማህበረ ምእመን ተግባር የሚሆነው
1. የኢትየጵያውያን ማህበረ ምእመንን ማገልገል
2. ስጦታዎችን በጥንቃቄ እንደ አስፈላጊነቱ እየታየ በህጋዊ መንገድ ምእመኑ በግልፅ በሚያውቅበት ሁኔታ መቀበል፣ በመያዝ ማሰራጨት፣ ይህም ስጦታ ሊሆን የሚችለው ኑዛዜ ውርስ፣ በግል ተነሳሺነት በፍቅር ስጦታዎችን የገንዘብና የቁሳቁስ እርዳታዎችን ለዚህ ተግባር በጥንቃቄ ማዋል።
3. ለተግባሩ የሚሆኑትን በቤተክርስቲያኒቱ ይዞታ በማድረግ መጠበቅ ወይንም አመቺ የሆኑ ንብረቶችን ህንፃዎችን የግል ይዞታዎችን እንደ አስፈላጊነቱ ለዚህ ተግባር መከራየት ይሆናል። ያለገደብ ውል በመግባት፣ በመተባበር፣ በማዘጋጀት ማንኛቸውም ህጋዊ የሆኑት ለዚህ ተግባር ውሎች መመስረትና ያለገደብ በተፈለገው መጠን ማናከናወን።
የቤተክርስቲያኒቱ ዶግማና ቀኖና በእግዚአብሔር ቃል የሚደገፍ ነው።ይህ ዶግማና ቀኖና በእምነት አንቀጽ ላይ ተጠቃልሎ ተብራርቷል፡፡
አንቀጽ 4 – ለትርፍ ያልተቋቋመ ሃይማኖታዊ ማህበረ ምእመን ህግ
ክፍል 1 – ገለልተኛና በራሱ ነፃ እንቅስቃሴዎች የሚተዳደር
ይህ ማህበረ ምእመን የተመሠረተው በቨርጂኒያ እንደማንኛውም ሃይማኖት ደርጅት በማህበረ ምእመንነት ከላይ ለተጠቀሰው ዓላማ የተቋቋመ ለትርፍ የማይሰራ ገለልተኛ ነፃ ድርጅት ነው። ከመሰረታዊ ክንዋኔዎች ውጪ በሆኑ እንቅስቃሴዎች የማህበረ ምእመኑ ድርጅት ጽሁፎችን በማሳተምና በማሰራጨት በህግ አውጭው ላይም ሆነ በአለው ህግ ላይ ጫና የሚፈጥር ተግባር የማያደርግ ነው። ማህበረ ምእመኑ ድርጅት በማንኛውም ምርጫ ዘመቻ የማይገባና ጫናም ለመፍጠር የማይሳተፍ ሲሆን ማንንም ለመንግስት ስልጣን መቀመጫ ለሚወዳደር ተመራጭ ወክሎ ወይም ተቃውሞ ህዝብ እንዲመርጥ ወይንም እንዳይመርጥ ለማድረግ የትኛውንም እርምጃ አይወስድም፣ እንዲሁም አይሳተፍም፡፡
የማህበረ ምእመን ድርጅት ከላይ እንደተጠቀሰው በአነስተኛም ሆነ በከፍተኛ መጠን በጽናት ከሚተገብረውና ከተጠራበት ተግባር ከተሰጠው ስልጣን ውጪ እንደማይሳተፍ አቋሙ ጽኑ ነው።
ክፍል 2 – የተግባር ክንዋኔ መንገዶች
ቤተክርስቲያኒቱ ተግባሮቿን የምታከናውነው በሚከተሉት መንገዶች ይሆናል
1. የእግዚአብሔርን ቃል በመስበክና በማስተማር
2. በአምልኮ በፀሎት በምስክርነትና በተሃድሶ ስብሰባዎች
3. የወንጌል ሥነጽሁፎችን በተለያየ ቅርጽና ይዘት በማዘጋጀት በማሰራጨት እንዲሁም በመጽሔት መልክ፣ በመንፈሳዊ መዝሙሮች፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መገልገያ ጽሁፎች፣ በድምፅ፣ በቪዲዮና በሬድዮ አገልግሎትና እንዲሁም ሌሎች በመሳሰሉት
4. ክርስቲያናዊ አገልግሎት ስልጠና በማዘጋጀትና በመስጠት እንዲሁም
5. መንፈሳዊ የህብረተሰብ አገልግሎቶች
6. በህብረተሰብ የልማትና የእርዳታ ስራዎች
አንቀጽ 5 – የቤተክርስትያን ተግባራት ክትትል
ቤተክርስትያንዋ ክርስቶስ ራስ መሆኑን እና መጸሐፍ ቅዱስ ዋናው መመርያዋ መሆኑን ታምናለች። (ቆላ፡ 1፡18፣ 2ጢሞ 3፡16) በዚህም መሰረት የቤተክርስትያንዋ ሽማግሌዎች ጉባኤ ከዲያቆናትና ከጠቅላላ ጉባኤ ጋር በመሆን የቤተክርስትያንዋን ተግባራት ይከታተላሉ፡፡ ቤተክርስትያንዋን የሚመለከት ማንኛውም ጉዳይ ላይ የቤተክርስትያንዋ ቁዋሚ አባላት ጉባኤ የበላይ አካል ነው፡፡ የሽማግሌዎች ጉባኤ አባላቱን በመወከል የቤተክርስትያንዋን ጠቅላላ የአስተዳደርና መንፈሳዊ ስራን ይሰራል፡፡
ክፍል 2 – ንብረትን ስለመጠቀም
የአንጾኪያ የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተክርስትያን ሃብትና ንብረት ለመንፈሳዊ ስራና ለማህበራዊ ግብረሰናይ አገልግሎት ብቻ ይውላል። ማንኛውም የማህበሩ የተጣራ ገቢ፣ ሃብትና ንብረት ማህበሩ በፈረሰ ጊዜ ወይንም በሌላ ምክንያት በተቁዋረጠ ጊዜ ለማንኛውም ግለሰብ ወይንም ሽማግሌዎች የግል ጥቅም መዋል አይችልም፡፡ በማህበሩ መፍረስ ወይንም መዘጋት ጊዜ የቤተክርስትያንዋ ሃብት እና ንብረት እንዲሁም ግዴታ በአሜሪካን የሃገር ውስጥ ገቢ ህግ (Internal revenue code section 501 (C) (3)) መሰረት ከቀረጥ ነፃ ወደሆነ ተመሳሳይ ድርጅት በስጦታ ይከፋፈላል፡፡
አንቀጽ 6 – ጠቅላላ ጉባኤ እና አባልነት
ክፍል 1 – አባል ለመሆን የሚሟሉ ስነስርዓቶች
ማንኛውም አባል መሆን የሚፈልግ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን እንደ ግል አዳኝ ተቀብሎ የመሰከረ፣ የውሃ ጥምቀትን የወሰደ፣ መጽሐፍ ቅዱሳዊ የሆነ የህይወት ስነምግባር ያሳየ እንዲሁም የቤተክርስትያንዋን መተዳደርያ ደንብና እና መመርያ የተቀበለ። ያመነበት መሆኑ በቤተክርስትያንዋ ሽማግሌዎች ከተጣራ በሁዋላ አባል መሆን ይችላል፡፡
ክፍል 2 – የአባልነት ስያሜ
የሽማግሌዎች ጉባኤ የአስተዳደር ተግባራቸውን በትክክልና በተገቢው መንገድ ለመወጣት
እንዲያመች በቤተክርስትያንዋ ውስጥ ሶስት አይነት የአባላት መዝገብ ይኖራል
1፡ ቋሚ አባላት
ከላይ በክፍል 1 የተጠቀሰውን የአባልነት መስፈርቶች ያሟሉ እና በወቅቱ በቤተክርስትያንዋ ቋሚ ሚና የሚጫወቱ ሲሆን እነዚህ ቁዋሚ አባላት ከታች በክፍል 3 በተጠቀሱት ጉዳዮች ላይ የመምረጥ መብት አላቸው፡፡ በሽማግሌዎች ጉባኤ ፈቃድ መሰረት ቋሚ አባላት በቤተ ክርስትያንዋ አስተዳደር እና አገልግሎት ውስጥ መሳተፍ ይችላሉ፡፡ በዚህ መተዳደርያ ደንብ ውስጥ ጠቅላላ ጉባኤ ወይም የጠቅላላ ጉባኤ ማለት የቋሚ አባላትን ጉባኤ ለማለት ነው፡፡
2፡ ተባባሪ አባላት
ከላይ በክፍል 1 የተጠቀሰውን የአባልነት መስፈርቶች ያሟሉ የሌላ ተመሳሳይ ቤተክርስትያን አባላት በልዩ ልዩ ምክንያት ለተወሰነ ጊዜ በመሃከላችን ተገኝተው ለመሳተፍ ወይንም ለማገልገል የሚገኙትን ያጠቃልላል፡፡ እነዚህ አባላት የመመረጥ መብት የላቸውም፡፡
ክፍል 3 – የጠቅላላ ጉባኤ አባላት የመምረጥ መብት ከቤተክርስትያንዋ የሽማግሌዎች ጉባኤ በሚቀርብ ማሳሰብያ መሰረት የቤተክርስትያንዋ ቋሚ አባላት በሚከተሉት ጉዳዮች ላይ የመምረጥ መብት አላቸው፡፡
1. ማንኛውም የጠቅላላ ጉባኤ አባል ለመምረጥም ሆነ ለመመረጥ እድሜው 18 እና ከዚያ በላይ መሆን አለበት
2. የቤተክርስትያንዋን አመታዊ ወጪ እቅድ(Budget)
3. ንብረትን ስለመግዛት እና የተያያዙ የእዳ ጉዳዮች
4. የቤተክርስትያንዋን ሙሉ ወይንም መጠነ ሰፊ የሆነውን ንብረት ስለመሸጥና መለወጥ
5. የቤተክርስትያንዋን መመስረቻ ወይንም መተዳደርያ ደንብ ስለማሻሻል
6. የቤተክርስትያንዋን ውህደት ወይንም ማፍረስ በሚመለከት
7. በማንኛውም ዓቢይ ጉዳይ ወይም የሽማግሌዎች ጉባኤ አምኖበት ወደ ጉባኤ በሚያቀርበው ዓቢይ ጉዳይ ላይ
ክፍል 4 – የአባላት ስንብት
ማንኛውም ቤተክርስትያንዋን በፈቃደኝነት ለቆ ወደ ሌላ ቤተክርስትያን ለመሄድ የወሰነ አባል የስንብት ደብዳቤ ሊሰጠው ይችላል፡፡ ራሱን በፈቃደኝነት ከአባልነት ያገለለ ወይም በሌላ ቤተክርስትያን አባል የሆነ የቤተክርስትያንዋ አባል ከቤተክርስትያንዋ የቋሚ አባላት መዝገብ ይሰረዛል፡፡
በሕይወት የሌሉ የቤተክርስትያንዋ አባላትም ከአባልነት መዝገብ ላይ ይሰረዛሉ፡፡ በቅጣት ስነስርዓት ውስጥ በአለ አባል ላይ የቤተክርስትያንዋ ሽማግሌዎች በውሳኔ አባሉን ከአባልነት መዝገብ ላይ የመሰረዝ ስልጣን አላቸው፡፡
ክፍል 5 – የቤተክርስትያን ቅጣት እና ተሃድሶ
የቤተክርስትያን ቅጣት እና ተሃድሶ ዓላማ በሃጥያት የወደቀ አባል ተሃድሶ አግኝቶ ከጌታ እና ከቤተክርስትያን ህብረት ጋር ወደሚኖረው ትክክለኛ መንገድ ለመመለስ እና የቤተክርስትያንን ቅድስና በህግ እና በተግባር ለመጠበቅ ነው። ይህቺ ቤተክርስትያን ለሰላምና ለእርቅ ተገቢ እና አስፈላጊ የሆነውን እርምጃ ሁሉ ትከተላለች፡፡ ማንኛውም የቤተክርስትያን አባል የቤተክርስትያንዋን ህግ ሲተላለፍ፣ እንዲሁም የሞራል ውድቀት እና የእምነት ግድፈት ሲገኝበት ወይንም የሃሰት ትምህርትን ሲያስፋፋ ከተገኘ የቤተክርስትያንዋ የሽማግሌዎች ጉባኤ ለግለሰቡ ተገቢ ማስታወቅያ እና የማጣራት እድል ከሰጡ በሁዋላ ከቤተክርስትያንዋ ህብረት የማግለል ወይም የአባልነት መብቱን(ለምሳሌ የመምረጥ መብት) ማገድ ይችላሉ።
የተላለፈው አባል በማቴዎስ 18፡ 15-17 መሰረት የቀረበለትን ተገቢ የንስሃ እድል ካልተጠቀመበት የሽማግሌዎች ጉባኤ ለተጠቀሰው አባል በፅሁፍ ጉዳዩን በጥልቅ የመመርመር ጊዜ እና እድል ለመኖሩ ማስታወቅያ መላክ ይኖርባቸዋል፡፡ ይህም ማስታወቅያ ከምርመራው አስር (10) ቀናት በፊት መድረስ ይኖርበታል፡፡ ጉዳዩን ካጣሩ በሁዋላ የሽማግሌዎች ጉባኤ ከኣባልነት መሰረዙን የሚገልጽ ደብዳቤ በመስጠት ወይም ሌላ ተገቢ የቤተክርስትያን ቅጣትን ማስተላለፍ ይችላሉ፡፡ የሽማግሌዎች ጉባኤ፡ አንድ አባል በቅጣት ከቤተክርስትያን ከተወገደ ለጉዳዩ ሚዛን በመስጠት ለጉባኤው ያስታውቃሉ፡፡
ክፍል 6 – ስብሰባዎች
1. የአባላት ዓመታዊ ስብሰባ በ January እና በ June ወራቶች ይካሄዳል፡፡ በነዚህ ስብሰባዎች ላይ በሽማግሌዎች ጉባኤ ጥያቄ መሰረት የአገልግሎት ክፍል ሃላፊዎች የጽሁፍ ዘገባ ያቀርባሉ፡፡
2. እንደ አስፈላጊነቱ የሽማግሌዎች ጉባኤ ተጨማሪ የአባላት ስብሰባን የሁለት ሳምንት ቅድሚያ ማስታወቅያ በመስጠት አባላቱን መጥራት ይችላሉ፡፡
3. ስብሰባዎቹን የሽማግሌዎች ጉባኤ ሊቀመንበር ሲመራ የጉባኤው ጸሃፊም የስብሰባዎቹ ፀሃፊ በመሆን ያገለግላል።
4. በዚህ መተዳደርያ ደንብ ውስጥ ከዚህ የተለየ ሁኔታ ካልተጠቀሰ በስተቀር መምረጥ በሚችሉ አባላት መሃከል ከግማሽ በላይ ድምፅ ብልጫ ያገኘ የውሳኔ ሃሳብ ተቀባይነትን ያገኛል፡።
ክፍል 7 – ምልዓተ ጉባኤ
ምልዓተ ጉባኤ ማለት በዚህ ደንብ ውስጥ በሌላ ሰራ ካልተጠቀሰ በስተቀር ለመምረጥ ተገቢውን መስፈርት ካሟሉት አባላት ውስጥ የአብዛኛው መገኘት ማለት ነው፡፡ በሽማግሌዎች ጉባኤ ጸሃፊ ምልዓተ ጉባኤው መሙላቱ ሳይረጋገጥ ማንኛውም ጉዳይ ለምልዓተ ጉባኤው ውይይት አይቀርብም፡፡
አንቀጽ 7 – ሽማግሌዎች
ክፍል 1 – የሽማግሌዎች ጉባኤ
ሽማግሌ በአባላት ጠቅላላ ጉባኤ ተመርጠው ለቤተክርስትያንዋ መንፈሳዊና አስተዳደራዊ ስራ የተሾሙ የቤተክርስትያንዋ ቋሚ አባላት ማለት ነው።
የሽማግሌዎች ጉባኤ ማለት በአባላት የተመረጡ ሽማግሌዎች በቤተክርስትያኗ አገልግሎት የሚያደርጉት ጉባኤ ነው። ይህ ጉባኤ የቤተክርስትያንዋን ዋና እረኛ ያካትታል ሆኖም ዋናው እረኛ በማይገኝበት ጊዜ ወይንም በተለየ የሽማግሌዎች ውሳኔ ላይ ያለ ዋና እረኛው ሊሰበሰቡ ይችላሉ። እንዳስፈላጊነቱ ሌሎች የቤተክርስትያኗ አገልጋዮችን በሽማግሌዎች ውሳኔ አክለው ሊሰበሰቡ ይችላሉ።
ክፍል 2 – ስልጣን እና ሃላፊነት
ሀ) የሽማግሌዎች ሃላፊነት
በቤተ ክርስትያንዋ እውነተኛ እና የጠራ ወንጌል መሰበኩን፣ መንጋው መጠበቁን እና የቤተክርስትያንዋን አጠቃላይ እንቅስቃሴን የመከታተልና የመፈጸም ሃላፊነት አለባቸው፡፡
1. ሽማግሌዎች የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት በሚገባ መሰጠቱን እና መተግበሩን የመከታተል ሃላፊነት ኣለባቸው
2. ሽማግሌዎች ግለሰቦችንና ቤተሰቦቻቸውን በግል በመጎብኘት፣ አባላትን በማማከር፣ ቤተክርስትያንን በማስተዳደር፣ በማስተማር፣ በምሳሌነት በመምራት፣ በተሃድሶ እና በአጠቃላይ የቤተክርስትያንዋን መላ አገልግሎት በበላይ የማስተዳደር ሃላፊነት አለባቸው፡፡
3. በማንኛውም ህግ በሚጠይቀው ህጋዊ ጥያቄ ላይ የሽማግሌዎች ጉባኤ የስራ አመራር ቦርድ ነው።
ለ) አጠቃላይ የህብረት ስልጣን (Corporate Authority)
በቨርጂንያ ግብረሰናይ ማህበራት ህግ እና በመተዳደርያ ደንቡ ላይ እንዲሁም በዚህ መተዳደርያ ደንብ ላይ ከተጠቀሰው ገደብ በስተቀር የቤተክርስትያንዋ ስራ እና ጉዳይ እንዲሁም ስልጣን በሽማግሌዎች ጉባኤ ይተዳደራል፡፡
ሐ) ልዩ ስልጣን፡
የአጠቃላይ ስልጣኑን በማይቃወም መልኩ፣ ከላይ የተጠቀሰው ገደብ እንዳለ ሆኖ የሽማግሌዎች ጉባኤ የሚከተለው ስልጣን አላቸው፡
- መላውን የቤተ ክርስትያን አገልጋዮች፣ ወኪሎች እና ተቀጣሪዎች የመሾምና የመሻር ስልጣን አላቸው፡፡ የቤተክርስትያንዋን ዋና እረኛ መሻር አስመልክቶ ግን ሁለት ሶስተኛው የጠቅላላ ጉባኤ አባላት በድምፅ ሊሽሩት ይችላሉ፡፡
- የቤተክርስትያንዋን ዋና ጽህፈት ቤት በቨርጂኒያ ውስጥ ስፍራ ለመቀየር፣ በሌላ ክፍለ ሃገር፣ ግዛት ወይም ሀገር ስር እንዲሰራ የሚያስፈልገውን መስፈርቶች ማሙዋላት እና ስራውን በቪርጂንያ ውስጥ ወይም ውጪ ለመስራት እንዲሁም ማንኛውም ስፍራ በቪርጂኒያ ውስጥም ይሁን ውጪ ተሰብስቦ የመምረጥ ስልጣን አላቸው፡፡
- የቤተክርስትያንዋን ማህተም የመቅረፅ፣ ተቀብሎ የማጽደቅ፣ እና የመጠቀም
- እንዲሁም ቅርፁን የመቀየር መብት አላቸው፡፡
- በህብረቱ ስም መበደር እና በብድሩ የተገኘውን ሀብት ለህብረቱ የማዋል መብት አላቸው፡፡ እነዚህም ብድሮች በቅድሚያ ለጉባኤ ቀርበው የድምፅ ብልጫ ማግኘት አለባቸው፡።
- የሽማግሌዎች ጉባኤ፣ ተጠሪነቱ ለጠቅላላው ጉባኤ የሆነ የቤተክርስትያንዋ የአስተዳደር መዋቅር ነው፡፡
- የሽማግሌዎች ጉባኤ አማኞች በሞራል ውድቀት፣ ህግ በመተላለፍ፣ በመናፍቅነት፣ እምነትን በማጉደል፣ በማመፅ እና በመሳሰሉት ሁኔታ ሲሳተፉ የመቅጣት ሃላፊነት አለባቸው፡፡ እንደ የበላይ አስተዳደር አካልነታቸው የሽማግሌዎች ጉባኤ አባላትንም የመቅጣት ስልጣን አላቸው፡፡
- ሽማግሌዎች የምክር አገልግሎትን ይሰጣሉ።
- ሽማግሌዎች ወንጌልን በመስበክ ላይ ይሳተፋሉ፡፡
- ሽማግሌዎች በቅዱስ ቁርባን አገልግሎት ይሳተፋሉ፡፡
- ሽማግሌዎች በአንቀፅ አምስት(5) የተጠቀሱትን ዝርዝር ሃላፊነቶች ይወጣሉ።
- የቤተክርስትያንዋን አገልጋዮች እና ተቀጣሪዎች ደመዎዝ፡ ጥቅማ ጥቅም እና የጉዞ ወጪ ይወስናሉ።
- ሽማግሌዎች የቤተክርስትያንዋን የአባልነት ጥያቄ የመመርመርና የመቀበል ሃላፊነት አለባቸው፡፡
መ) የሽማግሌነት መስፈርት
ማንኛውም ሽማግሌ በ1ኛ ጢሞቲዎስ 3፡1-7 እና በቲቶ 1፡5-9 ላይ የተጠቀሱትን መመዘኛዎች ያሟላ እንዲሁም በቤተክርስትያንዋ የእምነት አንቀፅና መተዳደሪያ ደንብ የሚያምን ፣ የሚደግፍ እና የሚገዛ መሆን ይኖርበታል፡፡
ሽማግሌነት ለመመረጥ ብቁ ለመሆን ለሁለት ዓመት ያህል ቁዋሚ አባል ሆኖ የቆየ መሆን አለበት።
1. የተመረጡ ሽማግሌዎች ቁጥር ከአምስት አስከ ዘጠኝ መሆን አለበት።
2. የሽማግሌዎች ጉባኤ አባላት አንድ የአገልግሎት ዘመን ሶስት ዓመት ነው። ማንኛውም ሽማግሌ በተከታታይነት ለሁለተኛ ጊዜ የሶስት ዓመት አገልግሎት ለመመረጥ ይችላል፡፡ ሆኖም በሁለተኛው የአገልግሎት ዘመን ፍፃሜ ላይ ለዳግም ምርጫ ለአንድ ዓመት ያህል በእጩነት መቅረብ አይችልም፡፡
3. በሽምግልና አገልግሎት ውስጥ ሳለ አንድ ሽማግሌ የተወሰነ የእረፍት እና የተሃድሶ ጊዜ መውሰድ ይችላል፡፡
ክፍል 4 ሽማግሌዎችን የመምረጥ ስነ ስርዓት
1. ለጠቅላላው ጉባኤ የአራት ሳምንት የፀሎት ጊዜ ይሰጣል።
2. አምስት አባላት የአሉበት አስመራጭ ኮሚቴ ይቁዋቁዋማል፡፡ ሁለቱ ከጠቅላላው ጉባኤ የሚመረጡ ቋሚ አባላት ሲሆኑ፣ ሁለቱ ደግሞ በአገልግሎት ላይ ከአሉት ሽማግሌዎች፣ አንድ ደግሞ ከዲያቆናት ቢሮ የተወከለ ይሆናል፡፡
3. አስመራጭ ኮሚቴው ከአባላት የተጠቆሙትን እጩዎች ለቤተክርስትያኑ ሽማግሌዎች ጉባኤ ያቀርባል፡፡
4. የሽማግሌዎች ጉባኤ 1ኛ ጢሞቲዎስ 3፡1-7 እና ቲቶ 1፡5-9 ያሉትን መመዘኛዎች በመጠቀም እጩው ብቁ መሆኑን እና ለአገልግሎቱ እውነተኛ ጥሪ ለመኖሩ ይመረምራሉ፡፡
5. ሽማግሌዎች የተጣሩትን ተመራጮች ወደ ጉባኤ ወስደው ከአባላት ተቃውሞ ከአለ በ
30 ቀን ውስጥ እንዲሰጣቸው ይጠይቃሉ፡፡ አባላት የቀረቡት እጩዎች በቂ አይደሉም ከአሉ ተጨማሪ ሰዎችን በውይይቱ ጊዜ ለመጨረሻ ጊዜ ማቅረብ ይችላሉ፡፡
6. አስመራጭ ኮሚቴው የተጣሩትን እጩዎች ለቤተክርስትያኑ አባላት በተቁዋቁዋመ በሶስት ሳምንታት ውስጥ ወደ ጉባኤ ይዞ ለማስመረጥ ይቀርባል፡፡
7. የሚቀርቡት እጩዎች ቁጥር ካለው ክፍት ቦታ ቁጥር ጋር በመተመን ከሚያስፈልጉት ተመራጮች ቁጥር በሁለት የሚበልጥ ይሆናል
8. ለሽማግሌነት ለመመረጥ፣ ከተገኙት መራጮች ውስጥ ከፍተኛውን ድምጽ ያገኙት ለሽማግሌነት ይመረጣሉ፡፡
ክፍል 5 – ቅጣት እና መገለል
ማንኛውም ሽማግሌ ሃላፊነቱን በተገቢው ሁኔታ መወጣት ካልቻለ ወይም የእምነት እና የሞራል ጥያቄ ውስጥ ከተገኘ በሽማግሌዎች ጉባኤ ውሳኔ መሰረት ሊቀጣ ወይም ሊወገድ ይችላል። ሽማግሌውን ለማግለል በሚደረግ የውሳኔ ሂደት ላይ የሚቀጣው ሽማግሌ ድምጽ የመስጠትመብቱን መጠቀም አይችልም፡፡ ይህንን የሽማግሌዎች ጉባኤ ውሳኔ ለማስታወቅ እና ለማፅደቅ በሰላሳ (30) ቀናት ውስጥ ልዩ የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ መጠራት አለበት። ጠቅላላ ጉባኤው በሁለት ሶስተኛ ድምፅ የሽማግሌዎቹን ውሳኔ መሻር ይችላል፡፡
ክፍል 6 – የሽማግሌዎች ስራ መልቀቅ
ማንኛውም ሽማግሌ የፅሁፍ ማስታወቅያ ለሽማግሌዎች ጉባኤ ሊቀመንበር በማቅረብ በማህበሩ መብት እና ሽማግሌው አባል የሆነበት ውሎች ላይ ተፅእኖ እስካላደረሰ ድረስ ስራውን መልቀቅ ይችላል። ከአገልግሎቱ በለቀቀ ወይም በተወገደ ሽማግሌ ምትክ በ 90 ቀን ውስጥ ተተኪ መመረጥ አለበት።
ክፍል 7 – ክፍት ቦታዎች
በሽማግሌዎች ጉባኤ የሚገኙ ክፍት ቦታዎች በሽማግሌዎቹ ውሳኔ መሰረት ልዩ ወይም መደበኛ ስብሰባ በመጥራት በ 90 ቀን ውስጥ ተተኪው በሽማግሌ አመራረጥ ደንብ መሰረት መመረጥ አለበት።
ክፍል 8 – ክፍያ
የቤተክርስትያንዋ ሽማግሌዎች ለሚሰጡት የሽማግሌነት አግልግሎት ያለ ክፍያ ያገለግላሉ።
አንቀጽ 8 – የሽማግሌዎች ጉባኤ ስብሰባ
ክፍል 1- ስብሰባዎች
የሽማግሌዎች ጉባኤ መደበኛ ስብሰባ ያደርጋል፡፡ ማንኛውም ሽማግሌ ከአንድ ሳምንት ያላነሰ ጊዜ በመስጠት አስቀድሞ እስካስታወቀ ድረስ ስብሰባ ለመጥራት መጠየቅ ይችላል። የሽማግሌዎች ጉባኤ ስብሰባ ላይ ከግማሽ በላይ አባላት ከተገኙ ምልዓተ ጉባኤው እንደተሙዋላ ይቆጠራል። ማንኛውም ውሳኔ በስብሰባው ከተገኙ አባላት መካከል በሚደረስ ከፊሊጵስዩስ 2፡2-8 ከሚገኘው በጋራ መሸናነፍ የመፅሃፍ ቅዱስ ሃሳብ ጋር በተጣጣመ መልኩ በተገኘ ሙሉ ድምፅ ይወሰናል፡፡ ሙሉ ድምፅ በስብሰባው ማግኘት ካልተቻለ ጉዳዩ ለሚቀጥለው መደበኛ ስብሰባ በድጋሚ ለመታየት ይቀጠራል። በቀጣዩ መደበኛ ስብሰባ ላይ ጉዳዩ የጉባኤውን አብላጫ ድምፅ ድጋፍ ካገኘ ይፀድቃል፡፡
ክፍል 2 – የጉባኤው ስብሰባ ሂደት እና ውሳኔ
1. የስብሰባው አካሄድ/ስነ ስርዓት
ሽማግሌዎቹ ሊቀመንበር ፣ምክትል ሊቀመንበር፣ ፀሃፊ፡ እና ገንዘብ ያዥን (Treasurer) በአባላት ከተመረጡት ሽማግሌዎች መሃከል በየሶስት ዓመት ይመርጣሉ። የቤተ ክርስትያኑ መጋቢ በሊቀመንበርነት ፣በምክትል ሊቀመንበርነት፣ በፀሃፊነት፡ ወይም በገንዘብ ያዥነት ማገልገል አይችልም፡፡
ሊቀመንበሩ የሽማግሌዎች ጉባኤን እና የጠቅላላው ጉባኤ ሊቀመንበር በመሆን ስብሰባዎችን ይመራል፡፡ ሊቀመንበሩ መገኘት ባልቻለበት ጊዜ ምክትል ሊቀመንበሩ ትክቶት ያገለግላል፡፡ ፀሃፊው የማንኛውንም የሽማግሌዎቹን ጉባኤ ስብሰባ እና ጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ቃለ ጉባኤዎችን በታማኝነት ዘግቦ በሰነድ ያስቀምጣል፡፡
ገንዘብ ያዡ የቤተክርስትያንዋን የገንዘብ አሰራር እንዲሁም የOዲት እና የግምገማ ወጤቶች ይከታተላል፡፡ የቤተክርስትያንዋ ተገቢ የሂሳብ መዛግብት መጠበቃቸውን በትክክል መውጣታቸውን ያረጋግጣል፡ በተጨማሪም በየሶስት ወሩ የቤተክርስትያንዋን የገንዘብ ነክ ነገሮች ዘገባ ለሽማግሌዎች ጉባኤ እና በዓመት ሁለት ጊዜ(በየስድስት ወር) ለጠቅላላው ጉባኤ ያቀርባል፡፡
2. የአብዛኛው ውሳኔ እንደ ሽማግሌዎች ውሳኔ ስለመቆጠሩ
ማንኛውም ምልዓተ ጉባኤው በተጠበቀበት ስብሰባ በተገኙ የሽማግሌዎች ጉባኤ አባላት በአብላጫ ድምፅ የተወሰነ ውሳኔ እንደ ሽማግሌዎች ጉባኤ ውሳኔ ይወሰዳል፡።
3. ከስብሰባ ውጪ ስልተገኘ የፅሁፍ ሙሉ ድምፅ ስምምነት
ማንኛውም የሽማግሌ ጉባኤ አባላት በግል ወይንም በጋራ በኤሌክትሮኒክስ በጽሁፍ ወይም በድምጽ ስምምነታቸውን ከገለጹ በዚህ ህግ መሰረት የተፈቀደውን ወይም የተጠየቀውን የሽማግሌዎች ጉባኤን ውሳኔ ጉዳይ ያለ ስብሰባ ማድረግ ወይንም መወሰን ይችላሉ፡፡
ይህ የጽሁፍ ስምምነት ከሽማግሌዎች ጉባኤ ቃለ ጉባኤ ውስጥ መካተት ይኖርበታል። በዚህ ሁኔታ ያለስብሰባ በጽሁፍ በተደረገ ስምምነት የተደረሰባቸው ጉዳዮች ሁሉ በጉባኤው ምልዓተ ጉባኤ ከተወሰኑ ጉዳዮች ጋር እኩል ተፈጻሚነት አላቸው፡።
አንቀጽ – 9 ዝርዝር የሽማግሌዎች ሃላፊነት
የቤተክርስትያንዋ የሽማግሌዎች ጉባኤ፡ ሊቀመንበር፣ ምክትል ሊቀ መንበር፣ ፀሃፊ እና ገንዘብ ያዥ ይኖረዋል፡፡
ክፍል 1 – የሽማግሌዎች ጉባኤ ሊቀመንበር
1. የሽማግሌዎች ጉባኤን በሊቀ መንበርነት ይመራል፡፡ የቤተ ክርስትያንዋን ስራ እና እንቅስቃሴ እየተቆጣጠረ ለሽማግሌዎች ጉባኤ ሪፖርት ያደርጋል።
2. በዚህ መተዳደርያ ደንብ እና በህግ የሚፈቀዱ የቤተክርስትያንዋን ስራዎች ያስተባብራል።
3. ዓመታዊ ዘገባ ለጠቅላላ ጉባኤው ያቀርባል፡፡
4. እንዳስፈላጊነቱ የሽማግሌዎች ጉባኤን በመወከል ከተለያዩ የአገልግሎት ክፍሎች ጋር ይመክራል፣ ይሰራል፡፡ ለሽማግሌዎች ጉባኤም አስፈላጊውን ሪፖርት በማቅረብ ውሳኔ ያስወስናል። ቤተክርስትያንዋን በሚመለከትና በሽማግሌዎች ጉባኤ የተወሰኑ ውሳኔዎች መፈፀማቸውን መከታተል ዋና ሃላፊነቱ ነው፡፡
ክፍል 2 – ምክትል ሊቀመንበር
ሊቀመንበሩ በማይገኝበት ጊዜ ወይም ሊቀመንበሩ ስብሰባውን ሊመራ ካልቻለ ወይም ሊቀመንበሩ ሊሰራ ፈቃደኛ በማይሆንበት ጊዜ ምክትል ሊቀመንበሩ ሃላፊ ይሆናል፡፡ በዚህም ወቅት ምክትል ሊቀመንበሩ ሙሉ የሊቀመንበርነት ስልጣን፣ ሃላፊነት እና ገደብ ይኖረዋል፡፡
ክፍል 3 – ፀሐፊ
1. በቤተክርስትያንዋ ጽህፈት ቤት ውስጥ በቅርብ የጸደቀውን የቤተክርስትያንዋን የመተዳደርያ ደንብ (Bylaw)፣ የእምነት ሰነድ(Statement of Faith) እና የህብረት ቃል ኪዳን(covenant) ማህተም አድርጎና ፈርሞ ያስቀምጣል፡፡
2. የሽማግሌዎች ጉባኤ እና የአባላት የምልዓተ ጉባኤ ስብሰባዎች በሚደረጉበት ጊዜ የአባላት ምልዓተ ጉባኤ መሙላቱን ያረጋግጣል፣ ቃለ ጉባኤዎችን፣ ውሳኔዎችን ፣ትእዛዞችን፣ ሃሳቦችን፣ በስብሰባው የተገኙ ሰዎችን ስምና አድራሻ በጽሁፍ አስፍሮ በመዝገብ ያስቀምጣል፡፡ ከጉባኤው የሚተላለፉ ውሳኔዎችን በህጉ መሰረት በጽሁፍ ያስተላልፋል፡፡ የቤተክርስትያንዋን መዝገብ እና ማህተም ይይዛል፡፡ በሰነዶቹም ላይ በመተዳደርያ ደንቡ ወይም በህግ መሰረት አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ማህተም ያደርጋል፡፡
3. የአባላትን ስምና አድራሻ የያዘ መዝገብ በቤተክርስትያንዋ ፅህፈት ቤት ውስጥ ይይዛል። አባልነታቸውን የለቀቁ ግለሰቦችን ከአባላት መዝገብ ላይ ዝርዝሩን እና ቀኑን በማስቀመጥ ይሰርዛል፡፡
4. የቤተክርስትያንዋን መተዳደርያ ደንብና የእምነት አንቀጽ፣ የአባላት ዝርዝር እና ቃለ ጉባኤዎችን እንዲያቀርብ በሽማግሌዎች ወይም በህግ ሲጠየቅ ያቀርባል፡፡
5. አጠቃላይ ለፀሃፊው ቢሮ የተወሰኑ ስራዎችን እና በህግ በቤተክርስትያንዋ ደንብ እና በሽማግሌዎች ጉባኤ እንዲሰራ የሚወሰንበትን የጽሕፈት ስራዎች ይሰራል፡።
ክፍል 4 – የሂሳብ እና የንብረት ሃላፊ
የሂሳብ እና የንብረት ሃላፊው የቤተክርስትያንዋን የፋይናንሰ አስተዳደር እና የኦዲት ተግባሮችን የበላይ ተመልካችና አስፈጻሚ ነው። ተገቢው የሂሳብ መዝገቦች በስርዓት መቀመጣቸውን በማረጋገጥ ለሽማግሌዎች ጉባኤ በየሶስት ወር የሂሳብ አያያዝ (Financial Report) ዘገባ ያቀርባል፡፡ ለጉባኤውም በዓመት ሁለት ጊዜ ዘገባውን ያቀርባል፡፡ በቤተክርስትያንዋ ደንብ መሰረት የሂሳብ እና የንብረት ሃላፊው የሚከተሉትን ይሰራል፡
1. የቤተክርስትያንዋን ገንዘብ በሃላፊነት የቤተክርስትያንዋ ባንክ ሂሳብ መግባቱን ያረጋግጣል።
2. በቤተክርስትያንዋ የሂሳብ አያያዝ መመርያ መሰረት የወጪ እና የገቢ ደረሰኞችን ይሰጣል።
3. ክፍያዎችን በውስጥ የሂሳብ አያያዝ መመርያ መሰረት ያካሂዳል፣ ይቆጣጠራል፣ ይመራል።
4. የቤተክርስትያንዋን ሂሳብ፣ ገቢ እና ወጪ፣ ንብረቶች፣ እዳዎች፣ ደረሰኞች፣ ክፍያዎች እና ሂሳብ አያያዝን በተመለከተ ሁሉ ያሉ ሰነዶችን ይይዛል።
5. የሂሳብ እና የንብረት ሃላፊው በተጠየቀ ጊዜ የሂሳብ መዝገቦችን ለቤተ ክርስትያንዋ ሽማግሌዎች እንዲሁም በህግ ሲጠየቅ ለህጋዊ ጠያቂው ያቀርባል፡፡
6. ማንኛውም ቁዋሚ አባል ለቤተክርስትያን የከፈለውን ሂሳብ ወይንም ለቤተክርስትያንዋ የሰጠውን ስጦታ ወይንም የቤተክርስትያንዋን የሂሳብ አያያዝ ሁኔታ ሲጠይቅ ይሰጣል ወይም ያቀርባል፡፡
7. መቅረብ ያለባቸውን የሂሳብ አያያዝ ዘገባዎችን በፊርማው ፈርሞ ያረጋግጣል፡፡
8. በአጠቃላይ የሂሳብ እና የንብረት ክፍል ስራዎችን በሽማግሌዎች ጉባኤ እንዲሰራ ሲጠየቅ ይሰራል፡፡ በህግ ወይም በቤተክርስትያንዋ መተዳደርያ ደንብ መሰረት መደረግ የሚገባቸውን የሂሳብ አያያዝ ስራዎች ሁሉ ያካሂዳል፡፡
ክፍል 5 ፡አጠቃላይ የሽማግሌዎች መማክርት ጉባኤ
- በቤተክርስትያኗ የምዕመናን ጉባኤ ለሽማግሌነት ተመርጦ የአገልግሎት ዘመኑን የጨረሰ ሽማግሌ የአጠቃላይ የሽማግሌዎች መማክርት ጉባኤ አባል ይሆናል።
- በአጠቃላይ ጉባኤው አዲስ የተመረጡ ሽማግሌዎችና የቤተክርስትያኗን እረኞችን የያዘ የምክክርና የአገልግሎት ማሰማርያ ጉባኤ ነው።
- አጠቃላይ የሽማግሌዎች መማክርት ጉባኤ በተመረጡት የወቅቱ የሽማግሌዎች ጉባኤ ሊቀመንበር ይመራል።
- ጉባኤው ሃሳብ በማቅረብና በአማካሪነት የወቅቱን የሽማግሌዎች ጉባኤን ይደግፋል።
- ጉባኤው የቀድሞ የቤተክርስትያኗ ሽማግሌዎችን በቤተክርስትያኑ ውስጥ በሽማግሌነት አገልግሎት የሚሰማሩበትን መንገድ ያመቻቻል።
- ይህ ጉባኤ በሽማግሌዎች ጉባኤ እንደአስፈላጊነቱ ለስብሰባ ይጠራል።
አንቀጽ 10 – ዲያቆናት
1. ተግባር እና አገልግሎታቸው:- ዲያቆናት በቤተክርስትያንዋ ማንኛውም
አገልግሎት ውስጥ በሽማግሌዎች ጉባኤ በሚሰጣቸው አገልግሎቶች ውስጥ ያገለግላሉ።
2. መመዘኛ:- ዲያቆናት በ 1ጢሞቲዎስ 3፡8-13 የአለውን መመዘኛ ማሟላት አለባቸው፡፡ የቤተክርስትያንዋ አባል የሆኑ ፣የመተዳደርያ ደንቡን መቀበል እና የአምነት ሰነዱን በሙሉ የተቀበሉ መሆን አለባቸው።
3. ሹመት:- የዲያቆናት አመራረጥ፣ ሹመት፣ መሻር፣ እና ስራቸውን በፈቃዳቸው መልቀቅ ለሽማግሌዎች ከተመደበው ስርዓት ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡
4. ብዛት:- የዲያቆናት ቁጥር ወሰን የለውም፡፡ እንደአስፈላጊነቱ በሽማግሌዎች ይወሰናል።
5. የአገልግሎት ዘመን:- የዲያቆናት የአገልግሎት ዘመን ሶስት ዓመት ሲሆን ዲያቆናት ያለገደብ በተደጋጋሚ በመመረጥ ማገልገል ይችላሉ፡፡
አንቀጽ 11 – የቤተክርስትያን አገልግሎቶች
1. መመዘኛ:- እረኛው መለኮታዊ ጥሪ ሊኖረው ይገባል (ኤፌሶን 4፡11፣ ሐዋ 20፡28)፡፡እረኛውፓስተሩ ከላይ የተቀመጠውን የሽማግሌዎች መመዘኛ (1ጢሞ 3፡1-7፣ ኤፌሶን 4፡11፣1ኛ ጴጥ 5፡1-4) የሚያሟላ መሆን አለበት፡፡ እረኛው በቤተክርስትያንዋ የእምነት አቅዋም የሚያምን፣ በመተዳደርያ ደንቧ የሚገዛ መሆን ይኖርበታል፡፡ እረኛው ከሌሎች ሽማግሌዎች በበለጠ በማስተማር እና በእረኝነት ሃላፊነቱ ሊተጋ ይገባዋል(ኤፌሶን 4፡11)፡፡ ተጨማሪ መመዘኛዎች በሽማግሌዎች ጉባኤ ይወሰናል፡፡
2. ሹመት:- የቤተክርስትያንዋ ሽማግሌዎች ለመጋቢነት የሚታሰቡ እጩዎችን የመፈለግ እና የማጣራት ሃላፊነት አለባቸው፡፡ በሽማግሌዎች ጉባኤ በ3/4 ተኛ ለእረኝነት እጩ ሆኖ የተመረጠውን ሰው በልዩ ስብሰባ ወይም በመደበኛ አመታዊ ስብሰባዎች ጉባኤው እንዲያፀድቀው ያቀርባሉ፡፡ የእረኛው ምርጫን ለማፅደቅ ከሁለት ሶስተኛ(2/3) ያላነሰ የድምጽ ብልጫ መገኘት አለበት፡፡
3. ስልጣን እና ሃላፊነት:- የመጀመርያ ሃላፊነቱ ቅዱሳንን ለአገልግሎት ስራ የእግዚያብሄርን ቃል በማስተማር ማስታጠቅ ነው (ኤፌሶን 4፡11-12). ተጨማሪ ሃላፊነቶች ከእረኛው ጋር በመመካከር በሽማግሌዎች ጉባኤ ይወሰናል፡፡ እረኛው ራሱን ችሎ በሽማግሌዎች ጉባኤ እንደ አንድ ሽማግሌ ይቀመጣል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ እረኛው በሽማግሌዎች ጉባኤ ውሳኔ መሰረት አገልግሎት ክፍሎችን የመቆጣጠርና ለሽማግሌዎች ጉባኤ ለውሳኔ ዘገባ የማቅረብ ሃላፊነት አለበት፡፡
4. የአገልግሎት ዘመን:- እረኛው አንድ ጊዜ ከተሾመ የተወሰነ የአገልግሎት ጊዜ ገደብ የለውም፡፡
5 ስንብት
5.1 እረኛው በራሱ ፈቃድ ከእረኘነት ሃላፊነቱ መልቀቅ ሲፈልግ የመልቀቅ ውሳኔውን ለሽማግሌዎች ጉባኤ ከመልቀቁ ከ 90 ቀን በፊት በፅሁፍ ማሳወቅ ይኖርበታል። የሽማግሌዎች ጉባኤም የእረኛውን የመልቀቅ ውሳኔ በ14 ቀናት ውስጥ ለጠቅላላ ጉባኤው ያስታውቃል።
5.2 የሽማግሌዎች ጉባኤ የእረኛውን አገልግሎት በየጊዜው እየመዘነና እየገመገመ እንደመጽሃፍ ቅዱስና በዚህ ደንብ ውስጥ እንደሰፈረው መመዘኛ በአግባቡ አልተወጣም ብሎ ባመነ ወይም ተጣርቶ የተረጋገጥ የስነምግባር ጉድለት በተገኘበት ጊዜ ሊያሰናብቱት ይችላሉ። የሽማግሌዎች ጉባኤ ውሳኔውን በ14 ቀናት ውስጥ ለጠቅላላ ጉባኤው ማሳወቅ ይኖርበታል። ሆኖም ጠቅላላ ጉባኤው የሽማግሌዎች ጉባኤ ያሳለፈውን የእረኛውን ማሰናበት ውሳኔ በ 2/3 ተኛ ድምጽ ውድቅ ማድረግ ይችላል።
ክፍል 2 – መለኮታዊ ጥሪ
- የሽማግሌዎች ጉባኤ በትጋት መለኮታዊ ጥሪ የአለውን እና መመዘኛዎችን የሚያሟላ ሰው በአባላት ምልዓተ ጉባኤ እንዲጸድቅ ያቀርባሉ
- በአንድ ጊዜ አንድ እጩ ብቻ በሽማግሌዎች ጉባኤ ይገመገማል፡፡ ይህም እጩ ወደ አባልነት ምርጫ ከመቅረቡ በፊት በሽማግሌዎች ጉባኤ ሁለት ሶስተኛ ድምፅ ማግኘት አለበት።
ክፍል 3 – ተጨማሪ እረኞች እና ሙሉ ጊዜ አገልጋዮች (Ministers) ዝርዝር የስራ ሃላፊነታቸው በቤተክርስትያንዋ የሽማግሌዎች ጉባኤ ይወሰናል፡፡ መመዘኛዎች፣ ሹመት እና የአገልግሎት ዘመናቸው ከዋናው መጋቢ ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡
ክፍል 4 – ሌሎች የቤተክርስትያንዋ ስራዎች
በቤተ ክርስትያንዋ ውስጥ ከመንፈሳዊ ስራ ውጪ ለሚያገለግሉ ሰዎች የሽማግሌዎች ጉባኤ አቀጣጠራቸውን፣ ሃላፊነታቸውን፣ መመዘኛቸውን፣ እንዲሁም ከስራ የሚሰናበቱበትን መመርያ እንደስራው አስፈላጊነት ያወጣሉ፡፡
ክፍል አምስት – የበላይ ተመልካች እና ውሳኔ ሰጪ
የሽማግሌዎች ጉባኤ የቤተክርስትያንዋን አገልግሎቶችና ከሌሎች ቤተክርስትያኖች እና ድርጅቶች ጋር የሚደረገውን ትብብርና ድጋፍ ሁሉ የበላይ ሆነው በመመልከት ውሳኔ ይሰጣሉ፡፡ የቤተክርስትያንዋ ስም ሌሎች የውጪ አገልግሎት ክፍሎችን ለመደገፍ ጥቅም ላይ የሚውለው የሽማግሌዎች ጉባኤ ሲፈቅድ ብቻ ነው፡፡
አንቀጽ 12 – የገንዘብ አያያዝ
ክፍል 1 – የዓመቱ የገንዘብ አያያዝ ጊዜ (Fiscal year)
የዓመቱ የገንዘብ አያያዝ ጊዜ (Fiscal year) በJanuary 1 ጀምሮ በDecember 31 ያበቃል።
ክፍል 2 – የገንዘብ አመዳደብ (Budget)
የቤተክርስትያንዋን የገንዘብ አመዳደብ (Budget) የቤተክርስትያንዋ የሽማግሌዎች ጉባኤ የማዘጋጀት ሃላፊነት አለበት፡፡ ከአመቱ የገንዘብ አያያዝ ጊዜ (Fiscal year) አስቀድመው የቤተክርስትያንዋን የገንዘብ አመዳደብ (Budget) ለቤተክርስትያን ሰራተኞች የሚከፈለውን ክፍያ እና ጥቅማ ጥቅሞች(Benefits) ዝርዝር በማዘጋጀት ለቤተክርስትያንዋ አባላት ያቀርባሉ፡፡ የቤተክርስትያንዋ አባላት የገንዘብ አመዳደቡን ካፀደቁ በሁዋላ የሽማግሌዎች ጉባኤ እንደ አስፈላጊነቱ ከጠቅላላው ፈቃድ ሳይወጡ ማስተካከል ይችላሉ፡፡
ክፍል 3 – ወጪዎች
በቁዋሚነት ከተፈቀዱት ወጪዎች ውጪ የሆኑ ወጪዎች በሚመለከተው የአገልግሎት ክፍል ጠያቂነት በሽማግሌዎች ጉባኤ እንዲፀድቁ ማቅረብ ይችላሉ፡፡ የሽማግሌዎች ጉባኤ ይህን ጥያቄ ቤተክርስትያንዋ ገንዘብ እንዳላት እንደሌላት በማመዛዘንና ቅድሚያ ከሚሰጣቸው ወጪዎች ጋር አስተያይተው ጥያቄውን ሊያፀድቁ ይችላሉ፡፡
ክፍል 4 – ዘገባ እና ቁጥጥር (Reports & Audits)
የቤተ ክርስትያን ገንዘብ ያዥ (Treasurer) ሽማግሌዎች በጠየቁት ጊዜ የገንዘብ ሪፖርት ያቀርባል። ለቤተክርስትያን ጉባኤም ቢያንስ በዓመት ሁለት ጊዜ የገንዘብ ዘገባ ወይም ሪፖርት ያቀርባል።
ከአባላት የተመርጡ ሁለት የሂሳብ አጣሪ ኮሚቴ አባላትም የቤተክርስትያኒቱን የሂሳብ አያያዝ አጣርተው የደረሱበትን ዘገባ በአመቱ የሂሳብ መዝጊያ ጊዜ ለጉባኤው ያቀርባሉ።
የሂሳብ ባለሙያም የቤተክርስትያንዋን የገንዘብ አያያዝ በቤተክርስትያንዋ የሂሳብ መተዳደርያ መሰረት በየዓመቱ ይመረምራል፡። ይህ ባለሙያ የቤተክርስትያኗ ተቀጣሪ ወይም ሽማግሌ መሆን የለበትም።
አንቀጽ 13 – የአባላት መደበኛ ስብሰባ
ክፍል 1 – ምልዓተ ጉባኤ
1. አብላጫው ቁዋሚ አባላት የተገኙበት መደበኛ ስብሰባ ሁሉ ምልዓት ጉባኤ ይሆናል።
2. ማንኛውም የአባላት ጉባኤ ስብሰባ ከመደረጉ በፊት ቢያንስ ከሁለት እሁድ ያላነሰ ተከታታይ ጊዜ ለስብሰባው ጥሪ በሽማግሌዎች በልዩ ልዩ መንገድ በይፋ መነገር አለበት።
3. ማንኛውም የአባላቱን ምርጫ የሚጠይቅ ስብሰባ ከሁለት ሳምንት በፊት አስቀድሞ ለአባላት እንዲዘጋጁና እንዲፀልዩበት በቂ መረጃ በመስጠት መገለፅ አለበት።
4. አዲስ ጉዳይ:- ማንኛውም የቤተክርስትያንዋ አባል የመወያያ ጉዳይ ከሽማግሌዎቹ ለአንዱ በማንኛውም ጊዜ ጉዳዩ በሽማግሌዎች ጉባኤ እንዲጠና፣እንዲገመገምና እንዲፀልዩበት የማቅረብ መብት አለው፡፡ ከሁለት ሳምንት በፊት አስቀድሞ ያልተነገረ አዲስ የመነጋገርያ ጉዳይ ወይም አጀንዳ በጉባኤው የስብሰባ ጊዜ ማቅረብ አይፈቀድም፡፡
5. አስፈላጊ ድምፅ፡ በሌላ ክፍል አስፈላጊው የማለፍያ ድምፅ ብዛት ካልተጠቀሰ በስተቀር፣ ለምርጫ የቀረበው ጉዳይ በአዎንታዊ ድምፅ እንዲያልፍ ከጉባኤው በአብላጫ ድምፅ(50% + 1) ማለፍ አለበት፡፡
ክፍል 2 – የመዋዋል ሃላፊነት
በቤተክርስትያንዋ ስም እና ቤተክርስትያንዋን ወክሎ ምንም አይነት ውል መፈራረምና የመግዛት ስልጣን ያለው የሽማግሌዎች ጉባኤ ብቻ ነው። እንደ አስፈላጊነቱ የሽማግሌዎች ጉባኤ አንድን ሽማግሌ ወይም የቤተክርስትያን ቁዋሚ ሰራተኛ እነርሱን ወክሎ ውል እንዲፈርም ሊፈቅዱ ይችላሉ፡፡
አንቀጽ 14 – አለመግባባት፣ ሃላፊነት እና ግዴታዎች
ክፍል 1 – አለመግባባት ሲፈጠር አፈታት
በዚህ የመተዳደርያ ህግ ሊፈቱ የማይችሉ አለመግባባቶች በአባላት መካከል፣ በፓስተሮች፣ በሽማግሌዎች፣ በቤተክርስትያንዋ ሰራተኞች እና በቤተክርስትያንዋ ውስጥ ሲፈጠር የመጽሐፍ ቅዱስን ምሳሌነት በተከተለ መንገድ ይፈታል፡፡ በዚህ መንገድ መፈታት ካልቻለ ህጋዊነት የአለው ክርስትያናዊ አስታራቂ የሽማግሌዎች ጉባኤ አቁዋቁሞ አለመግባባቱ እንዲፈታ ይሞከራል፡፡ ወገናዊ በአልሆነ አስታራቂ የዳኝነት አገልግሎት ውስጥም ሰዎች በመምረጥ ሽማግሌዎች ሊፈቱት ይሞክራሉ፡፡
ክፍል 2 – የሽማግሌዎች ሃላፊነት
የቤተክርስትያንዋ የኮሚቴ መሪዎች፣ ሽማግሌዎች፣ በግላቸው በማንኛውም የቤተክርስትያንዋ እዳ ወይም ግዴታዎች አይጠየቁም፡፡
ክፍል 3 – ለሰራተኞች ዋስትና
የሽማግሌዎች ጉባኤ ለቤተክርስትያንዋ ወኪሎች በቤተክርስትያን ጉዳይ ከተጠያቂነት ነጻ እንዲሆኑ ዋስትና ሊገዛ ወይም ሊያድስ ይችላል፡፡ ዋስትናው ህግን በመተላለፍ የሚነሳ ተጠያቂነትን አይጨምርም፡፡
አንቀጽ 15 – የቤተ ክርስትያን መዝገቦች
የቤተ ክርስትያንዋ የሽማግሌዎች ጉባኤ እና ሌሎችም የቤተክርስትያንዋ ክፍሎች ሙሉ እና የማይጠፋ የውሳኔ እና የሂሳብ መዝገቦችን በጽህፈት ቤት ያስቀምጣሉ፡፡ በህግ ሚስጥርነታቸው እንዲጠበቅ ከሚያስፈልጉ የአባላት ዝርዝር መረጃዎች በስተቀር ማንኛውም የቤተ ክርስትያንዋ አባል እነዚህን መዛግብት ለመመርመር ሊጠይቅና ሊመለከት ይችላል፡፡
አንቀፅ 16 – ማሻሻያዎች
በቤተክርስትያንዋ ሽማግሌዎች አቅራቢነት ይህ የመተዳደርያ ደንብ (Bylaw) ለዚህ ጉዳይ በተጠራ መደበኛ ወይም አስቸኩዋይ የአባላት ምልዓተ ጉባኤ ቀርቦ ሁለት ሶስተኛ አብላጫ የቁዋሚ አባላት ድምፅ ካገኘ ሊሻሻል ይችላል፡፡
እኔ የአንጾኪያ ኢትዮጵያውያን ወንጌላዊት ቤተክርስትያን ዋና ጸሃፊ ከላይ የተጠቀሱት የቤተክርስትያንዋ መተዳደርያ ደንብ እና የእምነት አንቀጽ በ April 5, 2009 ቀን በአባላት ጉባኤ ቀርቦ የጸደቀ መሆኑን እና ከዚህም ቀን ጀምሮ በስራ ላይ የዋለ መሆኑን በፊርማዬ አረጋግጣለሁ፡፡
……………………………….., ዋና ፀሃፊ
ፊርማ
ቀን እና ማህተም………………………………..