አንጾኪያ የኢትዮጵያውያን ወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን
ፍቺ፣ የእንደገና ጋብቻ እና ወደ አገልግሎት መመለስ
ይህ ሠነድ የአንጾኪያ ቤተ ክርስቲያን አባላት በፍቺና በሁለተኛ ትዳር ውስጥ ሲያልፉ፣ የአገልግሎትን አግባብ በተመለከተ ቤተ ክርስቲያኒቷ የምትጠቀምበት የውስጥ ደንብ ነው። ይህ ሠነድ የተመሰረተው፣ ቤተ ክርስቲያኗ በእምነት አንቀጿ ክፍል 11 ላይ፣ ስለ ቤተ ሰብ ባስቀመጠቻቸው ሦስት ዋና ሃሳቦች ነው።
1) ጋብቻ የአንድ ወንድ እና የአንዲት ሴት ሙሉ ዘመን አንድነት እና ቃል ኪዳን ነው (ዘፍ 2፥23-24፣ ማቴ 19፥4-6)።
2) ጋብቻ የሁለቱን አንድነት ኅብረት ያጸናል (ዘፍ 2፡25፣ ኤፌ5፡31-33) ።
3) በቀደምትነት የተመሰረተው ቤተ ሰብ የክርስቶስንና የቤተ ክርስትያንን አንድነት ለመመሰል ነው (ዘፍ 1፥ 28፣ ምሳሌ 5፥15-19፣ 1ቆሮ 7፥1- 5)።
የአንጾኪያ ቤተ ክርስትያን የእምነት አንቀጽ
ክፍል 11 – ቤተ ሰብ
እግዚአብሔር ቤተ ሰብን በመፍጠርና በመመስረት የህብረተ ሰብ መሰረት አድርጓል። ጋብቻ የአንድ ወንድ እና የአንዲት ሴት ሙሉ ዘመን አንድነት እና ቃል ኪዳን ነው (ዘፍ 2፥23-24፣ ማቴ 19፥4-6)። ጋብቻ የሁለቱን አንድነት ኅብረት ያጸናል (ዘፍ 2፥25፣ ኤፌ5፥31-33) ። በቀደምትነት የተመሰረተው ቤተ ሰብ የክርስቶስንና የቤተ ክርስቲያንን አንድነት ለመመሰል ነው(ዘፍ1፥28፣ ምሳሌ 5፥15-19፣ 1ኛቆሮ 7፥1- 5)። ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያንን እንዳፈቀራት ባልም ሚስቱን ያፈቅራት ዘንድ ታዟል።ቤተ ክርስትያን ለክርስቶስ አንደምትገዛ፣ ሚስትም ራሷን ለባልዋ ታስገዛ( ኤፌ 5፡22-23)።
ክፍል አንድ፦ፍቺ
“እግዚአብሔር ያጣመረውን ሰው አይለየው… ሚስቱን ፈቶ የሚያገባ ሁሉ በእርስዋ ላይ ያመነዝራል”
ማርቆስ 10፥ 9-12
“ያለ ዝሙት ምክንያት ሚስቱን ፈትቶ ሌላዩቱን የሚያገባ ሁሉ ያመነዝራል”
ማቴዎስ 19፥ 9
1.1 የአንጾያ ቤተ ክርስቲያን ጋብቻ የአንድ ወንድ እና የአንዲት ሴት ሙሉ ዘመን አንድነት እና ቃል ኪዳን በመሆኑ፣ በአማኞች መካከል ፍቺ እንዳይከስት የሚቻላትን ሁሉ ታደርጋለች። እግዚአብሔር በግልጽ የሚጠላውን ፍች፣ ቤተ ክርስቲያንም ትጠላለች። ስለዚህ ትዳር ከመፍረሱ በፊት፣ አማኞች የልብ ጥንካሬን በማስወግድ በይቅርታ ትዳራቸውን ያጸኑ ዘንድ ትመክራለች።
1.2 ሆኖም የሰው ልጅ የወደቀ እና እንደገና እየተሰራ ያለ ማንነት ስላለው ትዳሩ በተግዳሮት ውስጥ እንደሚያልፍ የታወቀ ነው። ከአቅም በላይ በሆኑ ምክንያቶችም የጋብቻ ቃልኪዳን ለመፍረስ ይጋለጣል። የአንጾክያ ቤተ ክርስቲያን እንደ እግዚአብሔር ቃል፣ የጋብቻ ቃል ኪዳን ወይም ትዳር
በሚከተሉት ሦስት ዋና ዋና ምክንያቶች ቢፈርስ ፣ ባለትዳሩ በነጻነት የሚመላለስበትን ሁኔታዎች ከዚህ በታች አስቀምጣለች፦
1.2.1 የትዳር ጓደኛ ከዚህ አለም በሞት በሚለይበት ጊዜ፦
“ያገባች ሴት ባልዋ በሕይወት ሲኖር ከእርሱ ጋር በህግ ታስራለችና ፣ ባልዋ ቢሞት ግን ስለባል ከሆነው ህግ ተፈታለች፣ ስለዚህ ባልዋ በሕይወት ሲኖር ለሌላ
ወንድ ብትሆን አመንዝራ ትባላለች፣ ባልዋ ቢሞት ግን ከህጉ አርነት ወጥታለችና ለሌላ ወንድ ብትሆን አመንዝራ አይደለችም።” ሮሜ 7 2-3
“ሴት ባሏ በሕይወት ሳለ የታሰረች ናት፤ ባልዋ ቢሞት ግን በጌታ ይሁን እንጂ የወደደችውን ልታገባ ነጻነት አላት” 1 ቆሮ 7፥39
1.2.2 የማያምን የትዳር ጓደኛ ትዳሩን ቢያፈርስ፣ ተፈቺው በትዳር ቃል ኪዳኑ አይታሰርም። ይህ አንቀጽ ተፈጻሚነቱ፣ የማያምን የትዳር ጓደኛ ላላቸው ነው።
“ የማያምን ግን ቢለይ ይለይ፤ ወንድም ቢሆን እኅት እንዲህ በሚመሰል ነገር አይገዙም፤”
1 ቆሮ7፡15 (አ.መ.ት)
1.2.3 አማኝ የሆነ የትዳር ጓደኛ፣ በዝሙት እና በእርኩሰት ሕይወት በመመላለስ፣ በቤተ ክርስቲያን ወደ ትዳሩ እንዲመለስ ሲመከር፣ ባይመለስና በእርኩሰት
ሕይወት እና በጋብቻ ከሌላ ሰው ጋር ቢጣመር እና ማግባቱ ሲመሰከር።
“ያለዝሙት ምክንያት ሚስቱን ፈትቶ ሌላይቱን የሚያገባ ሁሉ ያመነዝራል”ማቴዎስ 19፡ 9
ማሳሰቢያ፦ በጋብቻ ውስጥ ያለ ታማኝነት ሲፈርስ፣ ቤተ ክርስቲያን የመጀመሪያ ኃላፊነቷ፣ በስሯ ያሉትን መጠበቅ በመሆኑ፣ ትዳሩ የሚጸናበትን መንገድ ሁሉ
ትሻለች። ተጎጅዎችም ይጠገኑ ዘንድ የሚገባውን ሁሉ ታደርጋለች።
ክፍል ሁለት፦ እንደገና የሚደረግ ጋብቻ
“…ለመበለቶች ግን እላለሁ …ራሳቸውን መግዛት ባይችሉ ያግቡ” 1 ቆሮ 7፥8 -9
2.1 ከላይ በተጠቀሱት ሦስት ምክንያቶች ጋብቻ ሲፈርስ፣ መልሶም ማቆም ሳይቻል ሲቀር ፣ ተበዳዩ በቤተ ክርስቲያን የሚሰጠውን የቆይታና የምክር ግዜ
ከጨረሰ(ች) በኋላ፣ ዳግመኛ ማግባት ቢፈልጉ ቤተ ክርስቲያን ትፈቅዳለች።
2.2 ማንም ትዳሩን ከእግዚአብሔር ቃል ውጭ አፍርሶ፣ ድጋሚ ጋብቻን ለመፈጸም ቢሻ፣ ቤተ ክርስቲያን አታጋባም።
2.3 በእግዚአብሔር ቤት በመሪነት የሚያገለግሉ ሰዎች ምሳሌ ያለው ሕይወት ሊኖሩ ይገባቸዋል። ጋብቻቸውም የዚህ ነጸብራቅ በመሆኑ፣ መሪዎች ምሳሌ ያለው ትዳርና ቤተ ሰብ ሊኖራቸው ይገባል። ቤተ ክርስቲያን ይህንን የመሪዎች መለኪያ ታምናለች (1 ጢሞ 3፥1-6) ። ሆኖም፣ ትዳር ከላይ በተዘረዘሩት ምክንያቶች ቢፈርስ፣ ተበዳዩ ትዳር ለመመስረት፣ ቤተ ክርስቲያን በምታምንበትም መንገድ እና በክፍል 3.1 በተዘረዝረው ሂደት ውስጥ በማለፍ፣ ወደ መሪነት ለመምጣት፣ የሚያግደው ነገር አይኖርም።
ክፍል 3 :- ከፍቺ በሁዋላ የሚደረግ መንፈሳዊ አገልግሎት፤
3.1 በእነዚህ ከላይ በክፍል 1.2 በተጠቀሱት ሦስት ምክንያቶች፣ ትዳሩን መልሶ ለማቆም በማይቻልበት ሁኔታዎች ብቻ፣ የአንጾኪያ ቤተ ክርስቲያን በዚህ ሁኔታ
ውስጥ የሚያልፉ አባላቶቿን በምክር እና የቆይታ ጊዜ ውስጥ በማሳለፍ፣ እንዲሁም የሕይወት እና የአገልግሎት ምስክርነታቸውን በማየት፣ ደረጃ በደረጃ ወደ ተለያዩ
የአገልግሎት እርከኖች ታሰማራለች።
3.1.1 በትዳር ውስጥ ዝሙት ቢከሰት፣ አማኞች ኅጢአቱን በቸልታ ማየት የለባቸውም። ይልቁንም፣ ለቤተ ክርስቲያን በመንገር፣ ራስን ከአገልግሎት በፍቃደኝነት
በማግለል፣ ከቤተ ክርስቲያን የምክርን እርዳታ መሻት ይኖርባቸዋል። ቤተ ክርስቲያን በምትወስነው መሰረትም፣ የቆይታ ጊዜ ያስፈልጋቸዋል። በትዳር ተበዳይ የሆነው
ሰው የሚወስደው ቆይታ፣ ካጋጠመው ቁስል የሚያገግምበትና የሚፈውስበት ጊዜ እንዲኖረው በማሰብ ብቻ ይሆናል።
3.1.2 ትዳሩን በምክር መልሶ ማቆም ካልተቻለ ወይም ትዳሩ በፍቺ ከተጠናቀቀ፣ ቤተ ክርስቲያን ትዳሩን ፈልጎ ሳለ ተትቶ የተኬደውን ሰው ነጻ ታደርጋለች ።
ሆኖም ወደ አገልግሎት ከመመለሱ ወይም ከመግባቱ በፊት የክርስትና ሕይወቱ በሚታይበት እና በሚፈተሽበት ውሱን አገልግሎቶች ውስጥ ታሰማራለች። በመቀጠልም ደረጃ በደረጃ፣ የሕይወት ምስክርነቱን ዐይታ፣ በሁሉም አገልግሎቶች ሊሰማራ ይችላል በማለት በሽማግሌዎች ጉባኤ ውሳኔ መሰረት ታሰማራለች።
ክፍል 4፡ ከፍቺ በሁዋላ የሚደረግ የጋብቻ ቃልኪዳን እና ሠርግ
4.1 የአንጾኪያ ቤተ ክርስቲያን በእምነት አንቀጿ መሰረት “ጋብቻ የአንድ ወንድ እና የአንዲት ሴት ሙሉ ዘመን አንድነት እና ቃል ኪዳን በመሆኑ”፣ በመጽሐፍ
ቅዱስ ከተዘረዘሩት ምክንያቶች ውጭ የሚደረግን ሁለተኛ ጋብቻ ቤተ ክርስቲያኒቷ አታበረታታም።
4.2 በክፍል አንድ በተጠቀሱት ሦስት መለኪያዎች መሰረት ጋብቻቸው በራሳቸው ጥፋት አለመፍረሱ የተረጋገጠ አባላት እንደማንኛውም አባል ቤተ ክርስቲያን የጋብቻ ቃል ኪዳናቸውን ታከናውናለች ።
4.3 ቤተ ክርስቲያን ከዚህ መመርያ ውጪ የሚደረጉ ፍቺዎችን፣ ጋብቻዎችን ወይም ድጋሚ ጋብቻዎች ሲከሰቱ የዲሲፕሊን እርምጃዎችን ትወስዳለች።
ይህ ደንብ በአንጾክያ ቤተክርስትያን የሽማግሌዎች ጉባኤ ተዘጋጅቶ በጁን 19፣ 2025 ከታች በተዘረዘርው የቤተክርስትያኗ የሽማግሌዎች ጉባኤ ሙሉ የድምጽ
ስምምነት የቤተክርስትያኗ መመርያ ደንብ እንዲሆን ተደርጓል።
የአንጾክያ ቤተ ክርስቲያን የሽማግሌዎች ጉባዔ
1፡ ኮነ ፍሥሓ፡ ሊቀ መንበር
2፡ እመቤት ዥቃለ፡ ምክትል ሊቀ መንበር
3፡ ብሌን አበበ፡ ዋና ጸሃፊ
4፡ አክሊሉ ተስፋው፡ የሂሳብ ሹም
5፡ ዮሐንስ መሐመድ(ቋሚ መጋቢ)
6: ወርቅነህ ደርቤ (ቋሚ መጋቢ)
ብሌን አበበ
የአንጾክያ ቤተ ክርስትያን የሽማግሌዎች ጉባኤ ዋና ጸሃፊ
Signature/ፊርማ
Date/ቀን
June 19, 2025
